እሑድ 19 ኤፕሪል 2026
05:10:17 ከሰዓት UTC+3 - Addis Ababa
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ

ጎግል ክሮም አዲስ የደህንነት መከላከያ ሥርዓት አስተዋወቀ

2 ደቂቃ ንባብ
ጎግል ክሮም አዲስ የደህንነት መከላከያ ሥርዓት አስተዋወቀ
ከመሣሪያ ጋር የተቆራኘ የቆይታ ማረጋገጫ (Device Bound Session Credentials) ተብሎ የሚጠራው ይህ አዲስ አሰራር፣ በተለይ የሰዎችን የድረ-ገጽ ቆይታ መረጃዎች #Cookies በመስረቅ የሚፈጸምን የሳይበር ጥቃት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ጎግል ክሮም የግል መረጃ መንታፊዎችን ጥቃት የሚመክት አዲስ የደህንነት መከላከያ ሥርዓት አስተዋወቀ፡፡

ኩባንያው ያስትዋወቀው የጎግል የደህንነት ተመራማሪዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ከሚመነትፉ ሶፍትዌሮች #Infostealers ለመከላከል የሚያስችል ነው። 

ከመሣሪያ ጋር የተቆራኘ የቆይታ ማረጋገጫ (Device Bound Session Credentials) ተብሎ የሚጠራው አዲስ አሰራር፣ በተለይ የሰዎችን የድረ-ገጽ ቆይታ መረጃዎች #Cookies በመስረቅ የሚፈጸምን የሳይበር ጥቃት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ታስቦ መዘጋጀቱ ተመላክቷል። 

ኩኪዎች አንድን ድረ-ገጽ ሲጎበኙ ድረ-ገጹ ስለ እርስዎ መረጃ እንዲያስታውስ (ለምሳሌ የይለፍ ቃል ሳይጠይቁዎት እንዲቆዩ ወይም የመረጡትን ቋንቋ እንዲይዝ) በብሮውዘርዎ አማካኝነት በኮምፒዩተርዎ ላይ የሚቀመጡ ትናንሽ የመረጃ ፋይሎች ናቸው። 

ምንም እንኳ እነዚህ ፋይሎች ለድረ-ገጾች ቅልጥፍና አስፈላጊ ቢሆኑም፣ እስካሁን ባለው አሰራር ሌቦች አንዴ የእርስዎን "ኩኪ" (ወደ አካውንትዎ ለመግባት የሚያገለግል ዲጂታል ፈቃድ) ከሰረቁ፣ የእርስዎን የይለፍ ቃል ሳያስፈልጋቸው ወደ ግል ማህበራዊ ገጾችዎ ወይም የባንክ አካውንትዎ መግባት ይችላሉ።

አዲሱ ቴክኖሎጂ ይህንን ክፍተት የሚደፍነው የእርስዎን የድረ-ገጽ ቆይታ ከሚጠቀሙበት ኮምፒዩተር ሃርድዌር ጋር በጥብቅ በማቆራኘት ሲሆን፥ ሲስተሙ በመሣሪያዎ ውስጥ ብቻ የሚቀመጥና ሊሰረቅ ወይም ሊቀዳ የማይችል ልዩ "ዲጂታል ቁልፍ" ይፈጥራል መባሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ይገልጻል።

በዚህም ምክንያት መረጃ መንታፊዎች የእርስዎን ኩኪዎች ቢሰርቁ እንኳ፣ ያ ልዩ የሃርድዌር ቁልፍ በሌላው ማሽን ላይ ስለማይገኝ የተሰረቀው መረጃ ወዲያውኑ ዋጋ ቢስ ይሆናል። 

ይህም ሌቦቹ ወደ አካውንትዎ እንዳይገቡ በማድረግ አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያዳክመው ተገልጿል።

አገልግሎቱ በአሁኑ ወቅት በChrome 146 እና 147 ስሪቶች ላይ ለዊንዶውስ #Windows ተጠቃሚዎች በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ ለማክ #macOS ተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ታውቋል። 

በመሆኑም የክሮም ተጠቃሚዎች የብሮውዘር ስሪታቸውን በማዘመን #Update የዚህ አዲስ የደህንነት መከላከያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይመክራሉ።   


ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንሳይንስና ቴክኖሎጂ

0 አስተያየቶች

ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!