
በብዝኃነቷ ሀብታም የሆነችው አገራችን 2018ን አዲስ ዓመት ብላ በይፋ ከተቀበለች ወራት ብታስቆጥርም፤የየራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ባህል ያላቸው ሕዝቦቿ አዲስ ዓመታቸውን እንደየራሳቸው ባህል ያከብራሉ፡፡
ባለፉት ወራትም በርካታ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አዲሱን ዓመታቸውን ሲቀበሉ ነበር፡፡አሁን ደግሞ ተራው የሲዳማ ነው፡፡
የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ‘ፍቼ ጫምባላላ’ በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች በድምቀት መከበር ጀምሯል።
ፍቼ ጫምባላላ ለአገራዊ መግባባት፣ ለአንድነትና ለሰላም ጉልህ አበርክቶ ያላቸውን እሴቶች አቅፎ የያዘ በዓል ነው፡፡
በዓሉ ከ11 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ያስቻሉትም የእርቅ፣ የሰላምና የአንድነት እሴቶቹ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
የበዓሉ ዝግጅት አካል የሆነው ‘ኡሱራ’ የተሰኘው የሲዳማ ብቁ አረጋዊያን (ጭሜየ) የሚይዙት የጾም ሥርዓት ከበዓሉ ቀደም ብሎ ባሉ ቀናት የሚከናወን ነው፡፡ይህም ስላለፈው በደል ንስሃ የሚገባበትና መጪው ጊዜ የሰላም እንዲሆን የመማጸኛ ወቅት መሆኑ ባህሉ አዋቂዎቸ ያስረዳሉ፡፡
በ ‘ኡሱራ’ ከሚከወኑ ሥርዓቶች አንዱ የተጣሉ ሰዎችን ማስታረቅ ነው፤ ይህም ሰዎች ተጣልተው ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገር የለባቸውም በሚል እሳቤ ይፈጸማል፡፡
የሲዳማ ብሔር የአገር ሽማግሌዎችና ባህል አዋቂዎች የእርቅ ሥነ ሥርዓት ‘አፊኒ’ ይሰኛል፡፡ይህም የሲዳማ የውይይት ባህል የሚገለጥበት ሁነት ነው እን አዋቂዎቹ ገለጻ፡፡
እርቅ፣ ውይይትና ፍትህን አቅፎ የያዘው ይህ ሥነ ሥርዓት በዳይና ተበዳይ ሀሳባቸውን የሚናገሩበትና ለመደማመጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ፣ዘመናትን የተሻገረ የሕዝቡ መገለጫ እሴት ነው፡፡
በሥርዓቱ የተካተቱት የመመካከር፣ የመደማመጥና የእርቅ እሴቶች እንደ አገራዊ ምክክር ላሉ የውይይትና የመፍትሄ መድረኮች ፋይዳ እንዳላቸውም ተመላክቷል፡፡
‘ሰላም’ የፍቼ ጫምባላላ አስኳል መሆኑን የሚገልጹት የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎች፥ ከእርቅ እሴትነቱ ባሻገር፤ የሰላምና የአንድነት በዓል መሆኑን ለፋና ተናግረዋል፡፡
ጭሜየ በመባል የሚታወቁት ሽማግሌዎች ከበዓሉ ቀደም ብሎ ኡሱራ የተሰኘውን ፆም በመግባት ለአገር፥ ለሕዝብና ለእንስሳት ጭምር ሰላም እንዲሰፍን ፈጣሪን ይማጸናሉ።
የሲዳማ ሕዝብ በአያንቱዎች እየተመራ በራሱ አቆጣጠር ዘመንን የሚለውጥበት የፍቼ ጫምበላላ በዓል በውስጡ ብዙ የእገር አንድነትና የሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ እሴቶች አሉት፡፡
በፍቼ ቀን እንኳን ሰው ዛፍም ክብር አለው፤ ዛፍ መቁረጥ የተከለከለ ነው፤ ሕጻናትን መግረዝም አይፈቀድም፡፡
”የፊጣራ ምሽት” በሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምበላላ በዓል ላይ ከሚከወኑ ሁነቶች መካከል አንዱ ሥርዓት ነው ።
ፊጣራ ፍቼ ጫምበላላ በፊት ላለፉት 15 ቀናት አባቶች በጾሞና ጸሎታ አሳልፈው፤ ጾማቸውን የሚፈቱበት ቀን ነው።በዚህ የጾም መፍቻ ሥርዓትም አባቶች በአንድ ሻፌታ (ቡርሳሜ የሚበላበት እቃ) ውስጥ ሁሉም በኀብረት ማዕድ ይቋደሳል፡፡
ይህም አዲሱ ዓመት አንድነት የሚጠናክርበትና ሰላም የሚበዛበት እንዲሆን ለመመኘት የሚከናወን ሥርዓት ነው፡፡
ቡርሳሜ ሲበላ ወተት አብሮ ይቀርባል፤ ይህን ወተት ደግሞ አባቶች በአንድ መጠጫ አብረው ይጠጣሉ ይላሉ የባህሉ አዋቂዎች፡፡
በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ተናፍቆ የሚጠበቀው ፍቼ ጫምባላላ የአብሮነትና የአንድነት በዓል እንደ መሆኑ ወንድ ሴት፣ ሕጻናት፣ አዛውንት፣ ሀብታም፣ ድሃ ሳይባል ሁሉም በጋራ የሚያከብረው በዓል ነው፡፡
የሲዳማ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ሕዝቦችም ጭምር በዓሉን በጋራ ያከበሩታል፡፡ የጋራ እሴት በማዳበር የባህል ልውውጥ የሚደረግበት ሁነት በመሆኑ፡፡
በዓሉ ለአካባቢ ጥበቃ ያለው አስተዋፅኦ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ካስቻሉት እሴቶች አንዱ ነው፡፡
በበዓሉ ወቅት ዛፍ አይቆረጥም፣ መሬት አይቆፈርም፥ አደን ስለማይታደን ሁሉም ተፈጥሮ ይከበራል፤ ያርፋል፡፡ ከብቶች አይታረዱም፡፡ እንዲያውም በአዲስ የግጦሽ ሣር ይለቀቃሉ።
በዚህም በዓሉ የሰው ልጆች በቻ ሳይሆን፤የቀንድ ከብቶችም ጨምር ሆኖ ይከበራል ማለት ይቻላል፡፡
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ እንደተናገሩት፤ የሰላምና የመቻቻል እሴትን በውስጡ የያዘው "ፍቼ ጫምባላላ" የሲዳማ አባቶች በአገር በቀል ዕውቀት ዘመንን መቁጠር የሚቻልበትን ጥበብ ለትውልድ ያቆዩት ነው ይላሉ።
በዓሉ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ እሳቤና በአዲስ ተስፋ በውስጡ የያዛቸውን እሴቶች በሚያጠናክር መልኩ ዛሬና ነገ እንደሚከበርም ተናግረዋል።
የቱሪዝምና የአገልግሎት ማዕከል የሆነቸውየክልሉ መዲና ሃዋሳ ከተማ በኮሪደር ልማት መድመቋ በዓሉን የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፤ በዓሉ ክልሉንና ከተማዋን ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር በማመላከት።
''ኑ ወደ ሲዳማ እንሂድ'' በሚል መሪ ሃሳብ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና አርቲስቶች የተሳተፉበት የቱሪዝም መዳረሻዎችና መልካም እሴቶችን እንደሚተዋወቁም አስታውቀዋል።
በዓሉ የባህል አልባሳት በተሻለ አማራጭና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን የሀዋሳ ከተማ ሻጮችና ሸማቾች አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡
በከተማው ባህል አልባሳት ገበያ በተለያዩ ዲዛይኖች የቀረቡ አልባሳትም ለበዓሉ ድምቀት ሆነዋል፡፡
የ"ቤተሰብ የባህል አልባሳት ማምረቻና መሸጫ" ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መቅደስ አስፋው የባህል አልባሳት ገበያ ዓመቱን ሙሉ ያለ ቢሆንም፤ በ"ፍቼ ጫምባላላ" በዓል ከወትሮው በተለየ መልኩ ይቀርባል ይላሉ።
ለበዓሉ ለሁሉም ሰው በሚመች መልኩ በተለያዩ ዲዛይኖች አልባሳትን አዘጋጅተው ማቅረባቸውን በመግለጽ፡፡አልባሳቱ የሸማቹን ኪስ በማይጎዳ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የ"ራማ የባህል አልባሳት ማምረቻና መሸጫ"ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ራሄል አበበ በበኩላቸው የባህል አልባሳቱን በሁሉም ዕድሜ ክልል ላሉ ለባሾች በሚመች መልኩ አዘጋጅቼ አቅርቤያለሁ ብለዋል፡፡
አልባሳቱ ከበዓሉ ውጭም እንዲለበሱ አድርገው በልዩ ዲዛይን እንዳዘጋጇቸውም አስረድተዋል።
በዓሉን በድምቅት ለማሳለፍ በመረጠችው ዲዛይን የባህል ልብስ ማሰፋቷን የተናገረችው ወጣት አንቺንአየሁ ገብሬ በበኩሏ በከተማው በተለያዩ ፋሽን ዲዛይኖች የተዘጋጁ አልባሳትን መመልከቷን ገልጻለች።
ይህም በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ የተለየ ድምቀትና ድባብ እንዲላበስ ማድረጉንና የአልባሳቱም ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን ለኢዜአ ተናግራለች፡፡
"ፍቼ ጫምባላላ" የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ መጠን ያሉንን ውብ ባህሎች፣ አልባሳትና አብሮነታችንን ለዓለም የምናሳይበት ነው ስትልም ገልጻለች አንቺንአየሁ።
በተሻለ አማራጭ ከቀረቡ የባህል አልባሳት መካከል የፈለጉትን መርጠው ለመግዛት ከሆኮ ወረዳ ሀዋሳ ከተማ እንደመጡ የገለጹት ሌላው ሸማች ደግሞ አቶ ባጢሶ ዎጤ ናቸው።
ለእርሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚሆኑ የባህል አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዓሉን ከቤተሰብ እንዲሁም ከአካባቢያቸው ሰዎች ጋር በአብሮነትና በድምቀት ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውንም፡፡ፍቼ ጫምባላላ።ለታላቁ የሲዳማ ሕዝብ በዓል፡፡
0 አስተያየቶች
ገና አስተያየት የለም። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ይሁኑ!